Wednesday, October 21, 2015

የኦሮሞ ትርክቶች (Oromo Narratives)



የኦሮሞ ትርክቶች (Oromo Narratives)

ኢትዮጵያንና ህዝቧን በጥልቀት ያጠኑት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በኦሮሞ ጥናት ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ባቀረቡት አንድ ፅሁፍ የኦሮሞ ልሂቃንን በተመለከተ ሶስት ዓይነት ትርክቶች (Narratives) እንዳሉ ገልፀው ነበር፡፡ እነሱም ባህላዊው ትርክት፣ የቅኝ ግዛት ትርክትና የኢትዮያዊነት ትርክት ናቸው፡፡ እስኪ በራሳችን መንገድ ትርክቶቹን እንቃኛቸው፡፡ 

ባህላዊው ትርክት (Traditional Narrative) የኦሮሞን ባህልና ማንነት በተመለከተ የሚቆረቆርና በአመዛኙ የኦሮሞ ባህላዊ የዴሞክራሲ ስርዓት በሆነው በገዳ ስርዓት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በእኔ የንባብ ልምድ ይህን ስርዓት በተመለከተ እስከጥግ የፃፉ ሰው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ ናቸው፡፡ ለአውሮጳም ሆነ ለኢትዮጵያ ስርዓት እንግዳ የሆነው የገዳ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት በአውሮጳውያን ፀሃፍት አድልኦ እንደተደረገበት በመተንተን በዴሞክራሲ ቀዳሚነቱን ያስረዳሉ፡፡

የቅኝ ግዛት ትርክት (Colonialist Narrative) ኦሮሞዎች በታሪክ ውስጥ እንደተበደሉና እንደተሰቃዩ የሚያትትና በምሬትና እምባ ላይ የሚያጠነጥን ትርክት (Lachrymose Narrative) ነው፡፡ በዚህ ትርክት ውስጥ የሚኒሊክ የግዛት ማስፋፋት ጉዳይ ሰፊ ቦታ አለው፡፡ በዚህ የሚኒሊክ ግዛት ማስፋፋት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ ዕይታዎችን ፕሮፌሰር መረራ በሶስት ይከፍሏቸዋል፡- የጭቆና፣ የአገር ግናባታ እና የቅኝ ግዛት ብለው፡፡ ጉዳዩን ከብሄራዊ ጭቆና ጋር የሚያያይዙት ወገኖች በአንድ በኩል፣ የአገር ግንባታ ሂደት አካል መሆኑን የሚናገሩት በሌላ በኩል፣ እና ኦሮሚያ በኢትዮጵያውያን ቅኝ ተገዝታለች የሚሉት በጫፍ በኩል ሆነው ክርክሩን ያጦፉታል፡፡ ፕሮፌሰር መረራ ጉዳዩን በቅኝ ግዛት የሚመለከቱትን እነኦነግን ሲወርፉ በሻዕቢያ የትግል ስልት የተማረኩ እንጅ የኦሮሞን ማንነት የሚያውቁ አይደሉም በማለት ነው፡፡ የኦሮሞንም ታሪክ ከጨቋኞችም ከተጨቋኞችም ውስጥ እንደሚካተት ያስረዳሉ፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በበኩላቸው ጉዳዩ ጥንታዊ የግዛት ማስፋፋት ዓይነት እንጅ የቅኝ-ግዛት ጉዳይ እንዳልሆነ በመተንተን ይህን ዕይታ በዩሮ-ሴንትሪዝም (Euro-centrism) ይከሱታል፡፡ ያም አለ ይህ በዚህ ትርክት ዙሪያ የሚገኙ ልሂቃን በኦሮሞ መሬትና ኃብት ላይ የሚያተኩሩ፣ ለአፋን ኦሮሞ ዕድገትና ኦሮሞዎች በኢተዮጵያ ለሚኖራቸው ፖለቲካዊ ውክልና የሚጨነቁ ናቸው፡፡

ሶስተኛው ትርክት (Ethiopianist Narrative) የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተጫወተውን ሚናና ከሌሎች ህዝቦች ጋር እንደ ድርና ማግ እንደተሳሰረና የኢትዮጵያን ማህበረሰብ እንደፈጠር የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ትርክት ኦሮሞዎች ስለራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያስተካክሉ የሚወተውት ነው፡፡ በዚህ ትርክት ውስጥ ብዙ ታሪካዊ ሂደቶች ይገለፃሉ፡፡ ሱስንዮስ፣ ባካፋ፣ ኢያሱ 2ኛ፣ ኢዮአስ፣ አሊ፣ ጉግሳ፣ ልጅ እያሱ፣ ወዘተ. በትርክቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚደመጡ ናቸው፡፡ አፄ ባካፋ ኦሮምኛ ይናገር እንደነበር፣ ኦሮምኛ የቤተ-መንግስት ቋንቋ ሆኖ እንደነበር፣ ኢያሱ 2ኛ ኦሮሞዋን ውቢትን እንዳገባ፣ የጁ ኦሮሞ ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን እንዳስተዳደረ፣ ኦሮሞዎች በዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታና አስተዳደር ውስጥ የነበራቸው ሚና፣ ወዘተ. ተደጋግሞ ይገለፃል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ከተለያዩ የአገሪቱ ህዝቦች ጋር ተዋህደውና ተሳስረው መኖራቸውን ያስገነዝባል፡፡ ይህን ትርክት ጠቅለል ባለ መልኩ ከጥንቱ ታሪካችን ጀምሮ ለመነካካት የሞከረው ባለፈው ክረምት የታተመው የታቦር ዋሚ “የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች” የተሰኘ መፅሃፍ ነው፡፡ መፅሃፉ በውገና ከሚከሳቸው ሰዎች በባሰ መልኩ ራሱ የውገና ድርሰት በመሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ በጥቂቱም ለማንበብ ያልሞከራችሁ ሰዎች ባታነቡት (ብታቆዩት) ይመከራል፡፡ ይህን ሶስተኛውን ትርክት ለመግለፅ ግን መፅሃፉን መጥቀስ ቀላል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ሶስቱ ትርክቶች የአሁኖቹን አክቲቪስቶች ይገልጧቸዋል? ከገለጧቸውስ የትኛው ላይ ሊካተቱ ይችላሉ?

እንግዲህ ሶስቱ የትርክት ክፍሎች የተለዩት በሶሲዮሎጂስቶች ቋንቋ እንደሃሳባዊ ጎራዎች (Ideal Types*) ነውና አንድ ሰው ከሶስቶቹ ውስጥ በአንዱ ወይም በሁለቱ አልያም በሁሉም ትርክቶች ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡

በእኔ እይታ የሶሻል ሜዲያውን የከበቡት ዋናዎቹ አክቲቪስቶች ከሶስተኛው ትርክት (Ethiopian Narrative) ላይ ቆመው የብሶት ትርክቱን (Lachrymose Narrative) የሚያራምዱ ናቸው፡፡ እየገነቡ ነው ሲባል እያፈረሱ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምናልባት ሌላ ትርክት የሚፈጠርበት የሽግግር ጊዜ ይሆናል፡፡ ወይም አዲሱን ምድብ ለመሳል ከብዶኝ ይሆናል፡፡ ለዚያ ይሆናል ነገራቸው የማይገባኝ፡፡ ይህን አዲሱን የአክቲቪስቶች መፍጨርጨር “የጃዋርያን ትርክት” (Jawarian Narrative) እንበለው ይሆን? ፡) “ከኦሮሞ ፖለቲካ ወደ ጃዋር ፖለቲካ” ያለው ማን ነበር?! 

ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያ ትቅደም!

*Ideal Types= በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ባህርያትን በመውሰድ ለንፅፅርና ለትንተና ያመች ዘንድ የምንፈጥራቸው ሃሳባዊ ጎራዎች ናቸው፡፡ የዚህ ዘዴ ፈጣሪ ሌላ ይሁን እንጅ ታዋቂው ሶሲዮሎጂስት ማክስ ቬበር ዋነኛ አቀንቃኝ ነው፡፡    
 

Sunday, October 18, 2015

ሰላማዊ ትግል

ሰላማዊ ትግል

በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሰላማዊ ትግል አማራጭ ተቀባይነቱ ባዶ እየሆነ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ “ምንም አታመጡም” በሚል ትዕቢት አገሪቱን ያለፓርላማ እየገዛ ነው፡፡ ኦናው ቤት የተከፈተ ጊዜ አንዲት ሴትዮ ተኝታ የሚያሳይ ምስል የፌስቡክን ሜዳ ሞልቶት ነበር፡፡ እኔ ሴትዮዋ ዕድለኛ ካለመሆናቸው ውጭ የሴትዮዋ ጥፋት አልታየኝም ነበር፡፡ ጉዳዩ እንቅልፍን የመቋቋምና ያለመቋቋም ጉዳይ ነው፡፡ እኔም ብሆን ልተኛ እችል እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ካሜራው ስላልያዛቸው እንጅ ሌሎች የተኙ ሰዎች አይጠፉም፡፡ በአጠቃላይ ሙሉ የፓርላማ አባላት ከእንቅልፍ ጋር እየታገሉ ጉባዔውን እንደጨረሱት መገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ ሴትዮዋ የትኛውን አጀንዳ እንዲከራከሩበት ነው መንቃታቸውን የፈለግነው? ያለቀለትንና የምታውቁትን ነገር ሰው ሲዘረዝርላችሁ እንቅልፋችሁ ካልመጣ እናንተ የእንቅልፍ በሽታ ተጠቂዎች ናችሁ፡፡ ሴትዮዋ ዕንቅልፋቸውን መቋቋም አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግም ግምገማ ካካሄደባቸው ግምገማው መሆን ያለበት ለምን በዘዴ እንዳልተኙ ነው፡፡ “መነፅር ለብሰው፣ ነጠላዎትን ጣል አድርገው ቢተኙ ምናለበት” ብሎ የሚገመግማቸው ይመስለኛል፡፡

የእኝህ ምስኪን ዕድለ-ቢስ ሴትዮ ጉዳይ የተነሳሁበትን ነጥብ አስረሳኝ፡፡ ወደነጥቤ ልመለስ፡፡

እንግዲህ ኢህአዴግ ምንም ዓይነት አማራጭ ሃሳብ የማይፈልግ ከሆነና ሁለንተናችንን አፍኖ መግዛት የሚፈልግ ፍፁም አምባገነን እየሆነ ከመጣ ሰላማዊ ትግል ምን ድረስ ያስኬዳል ነው ጥያቄው፡፡ እኔ የሰላማዊ ትግል አማራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ኃይሎችን ለስልጣን ያበቃል የሚል ሃሳብ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ከወንበሩ ውጭ ያለውን ስልጣን ለመጠቀም ያስችላቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ከወንበሩ ውጭ ያለው ስልጣን ምንድነው? ከወንበሩ ውጭ ያለው ስልጣን ብዙና ቀጥተኛ የፖለቲካ እርምጃ የሌለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ ህዝቡን ጎሰኛ ማድረግ ይፈልጋል፤ ህዝቡ ጎሰኛ እንዳይሆን በኪነ-ጥበቡ፣ በሚዲያው፣ በትምህርት ቤቶች ወዘተ የመረባረብ ስልጣን በእጃቸው ነው፡፡ መንግስት በቀጥታ ሁሉንም ነገር ሊቆጣጠር ስለማይችል የመንግስት እጅ የሚያጥርባቸውን መንገዶች እየፈለጉ የህዝቡን አስተሳሰብ፣ የአገር ፍቅር፣ የፖለቲካ ባህል፣ ወዘተ. መቀዬር ይቻላል፡፡ ይህን ስናደርግም ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መገንባት እንችላለን፡፡ ይህን የስልጣን ዘርፍ እንደኢህአዴግ ዓይነት የደንቆሮ ጥርቅም ቀርቶ ማንም በሳል ቡድን በአግባቡ ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግል አንዱና በአግባቡ ያልተነካው የትግል መስክ ይህ ነው፡፡

ሌላኛው መንገድ መንግስትን በተቻለ አቅም የማግባባትና ልቦናቸውን የማራራት መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በአግባቡ ተሞክሯል የሚል እምነት ፈፅሞ የለኝም፡፡ ከመንግስት አካላት ጋር በሰከነና በተረጋጋ መንገድ መነጋገር፣ ኢህአዴግ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ጋር በግል መገናኘትና መከራከር/መወያዬት፣ ተመሳሳይ የትብብር ስልቶችን መንደፍ፣ ወዘተ፡፡

ሶስተኛውና አዋጭነቱ ፈታኝ የሆነው ነገር ግን በኢትዮጵያ በአግባቡ ተሞክሯል ለማለት አሁንም የሚያስቸግረኝ መንገድ የጄን ሻርፕ መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ ህዝቡ ለመንግስት የሚሰጠውን ትብብር እንዲነሳው በማድረግ መንግስትን ስልጣን የሌለው ባዶ ቀፎ የማድረግ ስልት ነው፡፡ ይሄን ስልት አምባገነኖች ከተቃዋሚዎች በላይ የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከስር ከስሩ እየተከተሉ ሙከራውን ያከሽፉታል፡፡ በእኛም አገር አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም በቀላሉ ሲከሽፉ አይተናል፡፡ መክሸፋቸው ግን ከኢህአዴግ ነቄነት ብቻ ሳይሆን ከስልቶቹ አላዋጭነትም ይመነጫል፡፡ ስልቶቹን ወስዶ ከኢትዮጵያውያን ነባራዊ ሁኔታና የፖለቲካ ስነ-ልቦና አንፃር ማገናዘብና መስማማት ይጠይቃል፡፡ ይህን ስል ጉዳዩ በተግባር ሲወርድ ፈታኝ እንደሆነ አጥቼው አይደለም፡፡ ነገር ግን በአግባቡ ያልተሞከረን ነገር ውጤት እንዲሁ መቀበል ልክ ስላልሆነ ነው፡፡ “የወያኔን ምርቶች አትጠቀሙ” የሚል ድፍንና ስልት-አልባ ዘመቻ ማካሄድ የዚህን የትግል መንገድ ልክ አያሳዬንም፡፡

ማደማደሚያ

በአሁኑ የኢትዮጵያ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነጠላ የትግል አማራጮችን ማቅረብ የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ወንበር ለመገልበጥ የግድ ጠመንጃ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ነፍጥ ያነሱት ኃይሎች በዚህ በኩል ልክ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡

ከጠመንጃው ውጭ ያለው መሰረታዊ የትግል አማራጭ ውድቅ ከተደረገ ግን ወንበር ተገልብጦም የማይስተካከል ነገር ይበዛል እላለሁ፡፡ ወንበር ለመገልበጥስ የጠመንጃው አዋጭነት ምን ድረስ ነው? ይህን ጥያቄ ራሱን ችሎ በሰፊው ማዬት የተሻለ ነው፡፡

ሰላማዊ ትግልን መጠቀም የኃይል አማራጩን መቃወም አይደለም፡፡ ፈፅሞ!
አሁንም ሰላማዊ ትግል ያስፈልገናል!!

***

ይህን ፅሁፍ ፅፌ እንደጨረስኩ ስልኬ አንቃጨለ፡፡
“ሄሎ፣ ሰበር ዜና ሰምተሃል?” … የወዲያኛው ድምፅ
“አልሰማሁም” … እኔ
“ዞን ዘጠኞች ተፈትተዋል”
በፈንጠዝያ ውስጥ ሆኜ ደስታውን ለማክበር ተቀጣጠርን፡፡ ወደዚያው እየሄድኩ ነው፡፡
እንኳን ደስ አላችሁ!
(ሰውን ይሄን ያክል ጊዜ ያለኃጢያቱ አስሮ የሚፈታ እንዲህ አይነት ደግ መንግስት ከቶ የታለ ፡) )
የኃይለማርያም ንግግር ታወሰኝ፡፡ ሽብርተኞች ናቸው ብሎም አልነበር!

Sunday, October 11, 2015

ጨርቅና ባንዲራ



ጨርቅና ባንዲራ

ባንዲራንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ አስቀያሚ የማነኮር ስራ የጀመረው ሟቹ ጠቅላያችን ነው፡፡ አንደኛ ባንዲራን ወደጨርቅነት አወረደው፡፡ ቢያንስ ልብስና ጨርቅ እንኳን እንደሚለያዩ አያውቁም ነበር ማለት ነው፡፡ መጋረጃና ጨርቅ አይለያዩም እንዴ ጎበዝ? መቀነትና ጨርቅ አይለያዩም እንዴ ጓዶች? ታዲያ ጨርቁ ለተወሰነ ዓለማ ሲውል የጨርቅነት ትርጉሙን አውልቆ እንደሚጥል መረዳት እንዴት ያቅታል?

ባንዲራ ብዙ ነገር የያዘ ክቡር ነገር ነው፡፡ It’s sacred after all. ባንዲራን በእንዲህ መንገድ መግለፅ ታቦትን ከመሳደብ አይተናነስም፡፡ አገር፣ ታሪክ፣ እውነት፣…ባንዲራው ውስጥ አሉ፡፡
አሜሪካኖች የቀደዱት አንድ የፍልስፍና መንገድ አለ፡፡ “Symbolic Interactionism” ይባላል፡፡ መሰረቱ ከነቻርለስ ፒርስና ዊሊያም ጄምስ የPragmatism ፍልስፍና ነው፡፡ በአጭሩ ለመግለፅ ያክል እነዚህ ፈላስፎች እንደሚሉት እውነታ የሚገኘው በነገሮች ምንነት ላይ ሳይሆን ሰዎች ለነገሮቹ በሚሰጧቸው ትርጉም ላይ ነው፡፡ ለነገሮች በዕለት ከዕለት ህይወታችን ውስጥ የምንሰጠው ትርጉም እሱ ነው የነገሮች ዕውነት ማለት፡፡

ይህ ፍልስፍና በተለይም በማንነት ቀረፃ ሂደት ላይ በጣም ይሰራል፡፡ በተለይ ባንዲራና ተያያዥ የማንነት ምልክቶችን አንስተን ስናወራ እንደ ጋሽ መለስ ከጨርቅነቱ በላይ መመልከት ካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡ ባንዲራ ማለት የአገር ምልክት ነው፡፡ መለስ ባንዲራን ሲሳደብ አገራችን ነው የተሳደበው፡፡

ባንዲራን ከጨርቅ በላይ የማይመለከቱ ሰዎች ባንዲራን እንደበጀት ለየክልሉ ቢያከፋፍሉ፣ በባንዲራው ላይ ያሻቸውን ንቅሳት ቢያስቀምጡ፣ የባንዲራን ክብርና የሚፈጥረውን ስሜት ባይረዱ ብዙም አይገርምም፡፡ ባንዲራዬን አይቼ በስሜት የማላለቅስ፣ የማልፎክር፣ የማልጨፍር፣ ወዘተ ከሆነ ባንዲራው ባንዲራ አይደለም፡፡

ቀለሙ ምንም ይሁን የእኔነት ስሜት የሚፈጥር፣ ዜጋው በታሪኩና በማንነቱ እንዲኮራና እንዲፋቀር የሚያደርግና የማነሳሳት ስሜት የሚፈጥር ካልሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ከሁሉም በላይ ባንዲራ Inspirational Power ያስፈልገዋል፡፡

ታሪክን ክደህና ለክህደትህ ምልክት ነቅሰህለት ባንዲራ ልትፈጥር አትችልም፡፡ መለስ እውነቱን ነው፤ የእሱ ባንዲራ ጨርቅ ነው፡፡ ውስጤን አያነሳሳም፡፡ ባንዲራ የሚሰራው ከደምና ከታሪክ ነው፡፡
ብሄራዊ መግባባት ያልተፈጠረበትና ከህሊናችን ጋር በአንዳች ምትኃታዊ ኃይል ያልተሳሰረ ባንዲራ ባንዲራ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ስዕልና ቀለም የመቀያዬር ጉዳይ አይደለም፡፡ የመለስ አንደኛው ውርስ የባንዲራን ልዩ ኃይልና ትርጉም ማናጋቱ ነው፡፡ ባንዲራን በኮሚቴ መስራቱ ነው፡፡ ባንዲራን በስዕል ምርጫና በምክንያታዊ ትንታኔ ሊገልፀው መሞከሩ ነው፡፡

የዮናታንም ሙከራ ያው ነው፡፡ መለስ በወጣትነቱ እንዲህ ያደርገው ነበር! ፡)  

Wednesday, October 7, 2015

ዋዛና ቁምነገር



ዋዛና ቁምነገር

(ውብሸት ታደለ)

ማሳሰቢያ፡

ማህበረሰብን ወይም ባህልን  ተችቶ መፃፍ ዕዳ ነው፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ቢያንስ ግማሹ የማህበረሰብ ታሪክና ሁለንተና እከክ አለበት፡፡ ስለዚህ አልፎ አልፎ በምፅፋት ትችት ቀርቶ ዕድሜ ልኬንም ህዝቤንና ባህሉን ስተች ብኖር እከኩ አይራገፍም፡፡ ለውጥና መሻሻል የሚመጣውም በትችትና ትችትን ተከትሎ በሚመጣ ክርክር ነው፡፡ ስለዚህ የፅሁፍን ፍሬ ነገር አንብቦ ከመሟገት ይልቅ ማለቃቀስም ሆነ መሳደብ ወይም አዕምሮዬን ለማንበብ መሞከር ያስቀስፋል ፡) ያስቀስፋል ብያለሁና ማንም ይችን ሙከራ የሚሞክራት ሰው እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ፡)

***
ሃበሻ ዋዘኛ ነው፡፡

“ዋዛ” የምትለዋን ቃል ስፈልግ ያገኘኋት ከአቤ ቶክቻው “ዋዛና ቁም ነገር” የተሰኘ የኢሳት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ዋዛ ምንድነው? እኔ ይህችን ቃል በዋዛ አላያትም፡፡ ዋዛ የቸልተኝነትና የዘፈቀደ ድምፅ ናት፡፡ ዋዘኛ ሰው ህይወትን አቅልሎ ይመለከታል፤ ቁምነገር አጠገቡ አይደርስም፡፡ አቤ ቶክቻው የማይታረቁትን ነገሮች አንድ ላይ አመጣቸው…ዋዛና ቁምነገር፡፡ ዋዛ እና ቁምነገር አብረው አይሄዱም፡፡ ዋዛ የሰነፎች፣ የደካሞች፣ የመሃይማን መደበቂያ ነው፡፡

እና የማይገባኝ ነገር…

ፖለቲካን ያክል ቁምነገር ለማውራት ዋዛ ለምን ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ፖለቲካ ከነስሜቱና ወኔው የሚገለፅ ካልሆነ በፈገግታና በዘፈቀደ የምናወራበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ታዲያ ዋዘኞች ለምን በዙ? ዋዛ ዕውቀት አይጠይቅም፡፡ አንድ የሰፈር ጎረምሳ ሃያ አራት ሰዓት በባለስልጣኖቻችን ላይ ሙድ ሊይዝ ይችላል፡፡ ሊስቅና ሊያስቅ ይችላል፡፡ ፖለቲከኞቻችንን የሚፈትን፣ የፖለቲካችንን አቅጣጫ የሚወስን ቁምነገረኛ ሃሳብ ግን ማቅረብ አይችልም፡፡ ይህ ዕውቀትና ሃሳቢነትን ይጠይቃል፡፡

ከዋዛ ጋር ብዙ ጊዜ አብሮ የሚመጣው ቀልድ ነው፡፡ ቀልድ ጭቆናን የመለማመጃ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ በጭቆናው ላይ የሚቀልድ ህዝብ ከጭቆናው ሊላቀቅ አይችልም፤ በፍፁም፡፡ በዋዛ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ጭቆናን አቅልለን እንድናዬው ከማድረግ ያለፈ ዋጋ የለውም፡፡ ከጭቆና ለመውጣት ቁጡና አልቃሻ ብዕሮች ያስፈልጉናል፡፡ ያ ትውልድ ወደአገራችን ካስገባቸው እንግዳ ባህሎችና አስተሳሰቦች መካከል ቁምነገረኝነት አንዱ ነበር፡፡ ታዲያ የሚገርመው… የትውልዱ እርግማኖች አብረውን አሉ፤ በረከቶቹ ግን ወደመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ቁምነገረኝነት እንደአመጣጣቸው ተመልሰው ሄደዋል፡፡ ሴራ፣ ፍረጃ፣ ጎሰኝነት አጎዛ ተነጥፎላቸው ተቀምጠዋል፡፡

ዋዘኝነት እንደገና አገሪቱን ተረክቧል፡፡ እንደተመስገን ደሳለኝ የገዢዎቻችንን ልብ የሚያርበተብቱና የህዝብን ህሊና የሚያነቁ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡

በዚህ ዋዘኛ ህዝብ መሃል እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ማግኘት ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ ቢገኙም እንኳን ቁምነገረኛ ሆነው የመቀጠል አዝማሚያቸው ደካማ ነው፡፡ የማህበረሰቡም ሆነ የፖለቲካው ስርዓት ቁምነገረኞችን የሚያስተናግድበት ቦታ የለውምና፡፡

የዋዘኝነት አንዱ ምንጭ ኃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖት ይህችን ምድር የሚያያት እንደጊዜያዊ መቆያ ነውና የሰው ልጅ ፍሬያማ ስራ ሰርቶ ለማለፍና የበለፀገች አገር ለልጁ ለማስተላለፍ ህልም አይኖረውም፡፡ ህልሙ ሰማይ ቤት ነው፡፡ ዓለምን የዋናው ህይወት መሸጋገሪያ ድልድይ አድርጎ የሚመለከት ህዝብ ድልድዩ ላይ እየተራመደ ስለሚሰራው ነገር ግድ የለውም፡፡ ከድልድዩ ማዶ እስኪደርስ ድረስ ጊዜ መግደያ ያስፈልገዋል…ቀልድ፡፡

የዋዘኝነት ሌላኛው ምንጭ ኋላቀርነት ነው፡፡ በቁስም ሆነ በሃሳብ ያልበለፀገ ህዝብ ዋነኛ መዝናኛው ወግ ነው፡፡ አምስት ሳንቲም የሌለው ሰው ከጓደኛው ጋር ሆኖ ሲዝናና ሊያመሽ ይችላል…ወግ እየጠረቀ፡፡ ሀበሻም ሌላ የሚዝናናበት ቁሳዊም ሆነ ሃሳባዊ ስልጣኔ ስለሌለው ወግ ሲያሳምርና ቧልት ሲያነጉት ይውላል፡፡ ማታ እሳት ዳር ተኮልኩሎ “እንካ ስለካንቲያ” ይላል፡፡ በስድብ ሲዝናና ያመሻል፡፡ የዋዘኛ ህዝብ ባህል ስድብ ነው፡፡ 

የአውሮጳ ጉብልስ? ምናልባት ስዕል ሲስል ወይም ኤሌክትሮኒክስ ሲፈታታ ወይም ድራማ ሲመለከት ወይም መፅሃፍ ሲያነብ ሊያመሽ ይችላል፡፡

በኤርሚያስ ለገሰ መፅሃፍ ውስጥ የተጠቀሱት የባለስልጣኖቻችን ቀልዶች ዋዘኝነት በዚያኛውም ወገን የተትረፈረፈ እንደሆነና ምን ያክል ደማችን ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ እየተጫወተብንም ያለው እሱ ነው፡፡ ርሃብና ስደት እያላጋን እንዲህ ወግ ስናነብቅ ከዋልን ትንሽ ችጋራችን ቢላቀቅልን ምን እንሆን ነበር?

ቁምነገረኞች ሆይ የት ናችሁ?

Tuesday, May 26, 2015

ስትመርጥ የኖረች ሴት

ስትመርጥ የኖረች ሴት

(ውብሸት ታደለ)

ትረፍ ሲለኝ እንደ2002ቱ ምርጫ ሁሉ በዚህ መሳቂያ ምርጫም እጄን አላነካካሁም፡፡ ኢህአዴግ በቡጢ እንጅ በምርጫ እንደማይወድቅ ባውቅም የሰላማዊ ትግሉን የመጨረሻ ሙከራ ለመደገፍ አስቤ ካርድ ልወስድ ነበር፡፡ ሚካኤል በምህረቱ ዳሰሰኝና የውርደት ካርዱን ሳልቀበል ቀረሁ፡፡ ምናልባት ቀን ሲያልፍ ለልጄ በኩራት እነግረዋለሁ፤ “እኔ አባትህ ካርድ አልወሰድኩም ነበር” እያልኩ አወራዋለሁ፡፡

ያላደላቸው ወገኖቼ ካርዱን እንደዳረጎት እጅ ነስተው በመቀበላቸው በምርጫ ጣቢያው ተገኝተው ‘ይሆነኛል’ ያሉትን ጨጓራ በሽታን መርጠዋል፡፡ ከምርጫ ጣቢያው መልስም ወደ ጤና ጣቢያ እንዳዘገሙ ዘገባዎች ያመለክታሉ J

የመኢአድ ሊቀ-መንበር በክርክሩ ወቅት የተናገሩት ነገር አሁን ግልፅ እንደሆነላቸው መራጮቹ ለራሳቸው ተናግረዋል፡፡ ሊቀ-መንበሩ በክርክሩ ጊዜ ‘ህዝቡ በደም ግፊት ምናምን የሚጠቃው በሚደርስበት በደል እየተበሳጨ ነው’ ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ዶ/ር ቴወድሮስ ይህን ነገር በጤና ፖሊሲው ውስጥ እንዲካተትና በምርጫ ቦርድና በኢቢሲ ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን እንዲቀንሱ አደራ እንላለን፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ለስኪዞፍሬንያ (የዕብደት በሽታ) መንስኤ ሆኖ ስለተገኘ አሳብዶ ሳይጨርሰን በፊት የአዕምሮ ጤናን በተመለከተ በኢህአዴግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ ለዶ/ር ቴወድሮስ አደራ እላለሁ፡፡ መቼም ዶ/ሩ “የውጭ ጉዳይ አይለምደኝም” ብለው ወደጤናው ይመለሳሉ ብዬ ነው አደራውን ለእርሳቸው መስጠቴ፡፡ እንደሌሎቹ ነባር ጓዶቻቸው ‘በእልህ መንቦራጨቄን እቀጥላለሁ’ ካሉም መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፡፡ ያውም የአልመዳ ጨርቅ! J በነገራችን ላይ ኮሮጆውን ያመረተው አልመዳ ነው የተባለው እውነት ነው? እንዲያውም ኢህአዴግ ምርጫውን ያዘጋጀው ከምርጫው ሳይሆን ከኮረጆው የሚያገኘውን ትርፍ አስቦ ነው ይባላል J

ድሮ ድሮ ኮረጆ ሲባል ቶሎ ወደአዕምሯችን የሚመጣው የቆሎ ተማሪ ነበር፡፡ ኮረጆ የምፅዋት መቀበያ ዕቃ ነበር፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለወያኔ ኮረጆ ሲባል ትዝ የሚለን ኢህአዴግ ነው፡፡ አሁን ኮረጆ የልመና ሳይሆን የዝርፊያ ዕቃ ነው፡፡ ከተመፅዋቾች ይልቅ ሌቦችን ያገለግላል፡፡

ድሮ ድሮ ካርድ ሲባል ትዝ የሚለን ጤና ጣቢያ ነበር፡፡ ካርድ የፈውስ ትኬት ነበር፡፡ አሁን ግን ዕድሜ ለገዢዎቻችን ካርድ ሲባል ትዝ የሚለን ምርጫ ጣቢያ  ነው፡፡ አሁን ካርድ የህመም ትኬት ነው፡፡ በውርደት ስሜት ምክንያት ለሚመጣ የጨጓራና የዕብደት በሽታ ያጋልጣል፡፡ ይህን በሽታ ለሃኪም ከተናገራችሁ ደግሞ ከጤና ጣቢያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትዛወራላችሁ፡፡

በነገራችን ላይ አንድ ለአምስት አደረጃጀት በህመምተኞች ላይ አልተሞከረም እንዴ? በመራጮች ላይ ተሞክሮ እኮ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል፡፡ አንድ ሰው የአራት ሰው ድምፅ ይሰጣል፣ አንድ ሰው አራት ሰው ከምርጫ ጣቢያ ያባርራል፣ ወዘተ፡፡ እናንተዬ! እኔ የምፈራው ግን ወሲብ በአንድ ለአምስት ይሁን እንዳይሉን ነው ሃሃሃ አንድ ካድሬ ለአራት ሴቶች J

ጥርሴ ይርገፍ! አሁን ይሄ ከምርጫው በላይ የሚያስቅ ነገር ሆኖ ነው?!

…….

አንዲት ወዳጄ (ትደግዬ) በዚህ ወቅት አንድ የበዕውቀቱን ግጥም አስታውሳኛለች… “ስትፈጭ የኖረች ሴት”፡፡ በእርግጥም ስትፈጭ ኖራ በፈጨችበት ድንጋይ መቃብሯ የሚከደን ያች የገጠር እህታችን ስለዚህ ጉድ ምን ታውቃለች?!

እሷ የምታውቀው መፍጨት ነው፡፡ ገዢዎቿ ዱቄቷንም ድምጧንም ከከረጢቷ ይዘርፋሉ፡፡ ዱቄቷም ድምጧም የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ በሲሲፈስ ብርታት ሁሌም ዱቄት ትፈጫለች፤ ዱቄቱ ግን ቋቷን አይሞላም፡፡ በሲሲፈስ ብርታት ሁሌም ድምጧን ትሰጣለች፤ ድምጧ ግን ለገደል ማሚቶ እንኳን አይበቃም፡፡ … ስትመርጥ የኖረች ሴት!

“አታውቅም…
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማን እንደሚባሉ
ሹማምንት በሷ ስም ምን እንደሚሰሩ
አነሳሁት እንጅ እኔም ለነገሩ
በፖለቲክ ጥበብ ራስን ማራቀቅ
ምን ይጠቅማትና ጓያዋን ለማድቀቅ”

(ካልረሳሁት እንዲህ እያለ ነው ግጥሙ የሚቀጥለው)

(በእንዲህ መልኩ ነው ኢህአዴግም የሚቀጥለው)

ሙሉውን ግጥም በማንበብ ሙሉውን የምርጫ ሂደት ይከታተሉ J … “ከቋት ስስት እንጅ ዱቄት አይታፈስ”!!

ግን በዘንድሮው ምርጫ ማን ያሸንፍ ይሆን?  J J 

ተስቶት ኢህአዴግ ካሸነፈ ግን ፕ/ር መርጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ… እየተባለ ነው ሃሃሃ
…….



Sunday, May 17, 2015

ስደትና ፖለቲካ




ስደትና ፖለቲካ


(ውብሸት ታደለ)

ኢትዮጵያውያን ካለቅጥ በመሰደድ ቀደሚውን ስፍራ የምንወስድ ህዝቦች መሆናችንን ዓለምም ሆነ እኛው ራሳችን የምናውቀው ነው፡፡ በየአገራቱ የሚቀበሉትን መከራና ስቃይ የሚሰማው ህዝብ፣ በየጊዜው የወንድሞቹንና የእህቶቹን ሰቆቃ አስመልክቶ እሪታ የሚያሰማው ህዝብ፣ ከስደት የተመለሰው ህዝብ፣ … አሁንም ስደትን ይመኛል፡፡ ከስደት በታች የሆነች አገር ይዘናል፡፡ ለዚህ አሳፋሪ አገራዊ ሁኔታ የመንግስታችን መልስ ሁሌም ተመሳሳይ ነው፡፡… “የግንዛቤ ችግር”፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ይህንን መልስ በየቦታው ሲደጋግሙት ይሰማሉ፡፡ ጉዳዩም ደላሎችን በማሳደድ ሊፈታ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይህ የቆዬ የመንግስት አቋም እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ጉዳዩን በዋናነት የሚከታተለው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴርም ይህንኑ ሃሳብ ሲያራምድ አመታት ነጎዱ፡፡ 


አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፡፡ ከአንድ የክልል ባለስልጣን ጋር የሆነ ቦታ እንገናኛለን፡፡ ስለግል ጉዳዮቼ ስናነሳ ቆይተን ውጭ አገር ስለመሄድ ተነሳ፡፡ ይህ ባለስልጣንም ምክሩን ለገሰኝ፡፡ “አገር ውሰጥ ሰርቶ መለወጥ ምናምን ሲባል የእውነት እንዳይመስልህ፤ በቻልከው አቅም ማምለጥ ነው” ሲል ወቀሰኝ፡፡ ይህ ባለስልጣን በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኃላፊነት የሚሰራ ሲሆን በስደት ዙሪያ መግለጫ ሲሰጥ የሚውል ነው፡፡ ዶ/ር ቴወድሮስም በግል ቢያገኟችሁ እና የሚወዷችሁ ከሆነ ይህንን ምክር እንደሚደግሙላችሁ አትጠራጠሩ፡፡ 


ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓላማዎች ጥቂቶቹ ለዜጎች የስራ ስምሪት አገልግሎት መስጠት፣ የሰራተኞችን መብትና ደህንነት ማረጋገጥ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ ተቋም እንኳን ችግሩን ከስራ ስምሪት አንፃር ሊመለከተው አለመቻሉ ነው፡፡ ህዝብ በስራ እጦት፣ ባልተመጣጠነ ክፍያ፣ በለዬለት ድህነት አሳሩን እያዬ እነሱ “ግንዛቤ” የሚሉት ተረት ያወራሉ፡፡ የቻይና ካምፓኒዎች ውስኪ ይዘው ወደ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሲመላለሱ ማዬት ብርቅ አይደለም፡፡ ኃላፊዎችም የምስኪኑን ሠራተኛ ላብ በውስኪ ጠርሙስ ይጠጣሉ፡፡ እንዲህ እያዋረዱን ስለስደት ሊያስተምሩን ይፈልጋሉ፡፡ ባለስልጣኑ ስደት በሚመኝባት አገር ውስጥ ማነው ማንን ስለስደት የሚያስተምረው? 


አገራችን ከስደት ከፍታለች፡፡ 


በአንድ ወቅት ጌታቸው ረዳ የተባለው የኢህአዴግ ጡሩምባ ስለአንድ ኢህአዴግን ክዶ ውጭ ስለወጣ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ሲናገር ጉዳዩን ውጭ አገር ከመኖር ድሎት ጋር አገናኝቶት ነበር፡፡ ንግግሩን ስንተረጉመው አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ከስልጣኑ ይልቅ ውጭ አገር ሄዶ በጉልበቱ ሸቅሎ ማደር ይፈልጋል እንደማለት ነው፡፡ ምን ዓይነት የከፋ አገራዊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ ነው ባለስልጣኖቻችን ሳይቀሩ ለኑሯቸው መሻሻል ስደትን ይመኛሉ እስከማለት ያደረሰን? የጌታቸው ንግግር በተዋረደ አገር ውስጥ የመኖራችንን ሃቅ ሳይፈልግ የሚመሰክር ነው፡፡ አገሪቱ ምን ያክል የጥቂቶች ብቻ እንደሆነችም የሚያሳይ ነው፡፡


ከአረብ አገራት የተመለሱ ዜጎች ከስደት እንደመጡ መንገድ ላይ ችፕስ መሸጥ፣ ገላን መሸጥ፣ ወዘተ. ጀምረው አልሳካ ሲላቸው ወደስደታቸው እንደተመለሱ አውቃለሁ፡፡ በግሌ ብዙ እንዲህ ያደረጉ ዜጎችን አውቃለሁ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሴቶች ይህን ችጋር መቋቋም ሲያቅታቸው መሰደዳቸው ነው የግንዛቤ ችግር ማለት፡፡ የጉድ አገር!


ሰሞኑን ደግሞ በስንት ጩኸት የተመለሱትን ስደተኞች ማዕከላዊ እንዳጎራቸው ሰማን፡፡ እነሱም አገር አለን ብለው መጥተው ለማዕከላዊ ሲዖል ተዳረጉ፡፡ የግንዛቤ ትምህርቱን ማዕከላዊ ሊሰጧቸው ይሆናል ፡) ፡( የጉድ አገር!!


እንደእውነቱ ከሆነ ለኢህአዴግ የሚሻለው የዜጎች መሰደድ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ዜጎች ለስደት የሚከፍሉትን መከራ ስርዓቱን ለመጣል ይከፍሉት ነበር፡፡ ወደ ሰሃራ ከማዝገም ወደ ደደቢት ይሮጡ ነበር፡፡ 


የዚያ ትውልድና የዚህ ትውልድ የጋራ ጉዳይ ጭቆና ነው፡፡ 


ያ ትውልድ በጭቆናው በመማረር ወደአገሪቱ ጫካዎች ተሰደደ፡፡ ይህ ትውልድ በጭቆናው በመማረር ከጫካዎቻችን ማዶ ተሰደደ፡፡ በዚያኛውም ሆነ በዚህኛው ትውልድ ስደቶች ውስጥ ሞትና ስቃይ አለ፡፡ የዚያ ትውልድ ስደተኞች ጫካ ውስጥ ሆነው ስለጭቆናቸው ያወራሉ፤ የዚህ ትውልድ ስደተኞች ከጫካው ማዶ ሆነው ስለጭቆናቸው ያወራሉ፡፡ ይህ ትውልድ ወደ ጫካው ቢሰደድ ኖሮ ኢህአዴግ አለቀለት ማለት አልነበረም?!


ስለዚህ ለኢህአዴግ የዜጎች ስደት ይሻለዋል፡፡


ጥቂቶችም በሰላም ውስኪያቸውን ይጠጣሉ፡፡


ግፍ ሲሰሩ ይውሉና ግፋቸውን በውስኪ ይረሳሉ፡፡ ህዝቡም ግፍ ሲቀበል ውሎ ግፉን በአረቄ ይረሳል፡፡ አረቄ የማይጠጡትም የስደትን ፅዋ ይጎነጫሉ፡፡ ክፋቱ ስደት ግፍን አያስረሳም፤ እንዲያውም ያስታውሳል እንጅ፡፡


ከመሰናበቴ በፊት ዶ/ር ቴወድሮስን አንድ ሙዚቃ ልጋብዛቸው፡


“Open your eyes and look within
Are you satisfied with the life you are living?
.
.
We know where we are from we know where we are going”
-Bob